ሞመንተም ለኢትዮጵያ
የለውጥ አፋጣኝ እና የገጽታ ግንባታ ማህበር
ሀገር
ሀገር ከፖለቲካ ቡድን፣ ከሃይማኖት ወይንም ከሌሎች የግል
ጉዳዮች ሁሉ የበለጠ ዋጋ ያለው፣ የቀደሙ አባቶች እና እናቶች ተፈጥሮን አልምተው በቦታውም ላይ ሞተው አፈሩን ከስጋና ከአጥንታቸው
ቀላቅለው ያስረከቡን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ልዩ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ልጅ መከበሪያ እና ለዘለዓለም የሚጠበቅ የአደራ ገንዘብ
ነው:: የ http://www.selamta.net/hager.pdf ድረ-ገጽ ከመጽሐፈ ምሳሌ ሶስተኛ በመውሰድ የሀገርን ምንነት እንዲህ ሲል ገልጾታል:: “ሀገር በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በልምድ፣ በተስፋ፣ በደስታና በመከራ ተሳስሮ ብዝህነቱን ጠብቆ ተዋህዶ የሚኖር አንድ ወገን የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት የዓለም ክፍል ነው:: ሀገር ማለት አያት ቅድም አያት የተወለዱበት አድገውም በጀግንነት ከውጭ ጠላት እየተከላከሉ ለሕዝብና ለመንግስት የሚጠቅም ሥራ ሰርተው እድሜያቸው ሲደርስም ልጆቻችውን ተክተው የተቀበሩበት ጉድጓድ ነው:: በመወለድ እትብት፣ በመሞት አካል ከአፈሩ ጋራ ስለሚዋሐዱ የአገሩ አፈር የጥንት አባቶች እና እናቶች ደምና አጥንት የተቀላቀለበት ሕዝብ በላዩ የሚኖርበት ምድር ማለት ነው:: እግዚአብሔር ከምድርዋ ፍሬ ሕይወት እንዲገኝባት በማድረጉ ሀገር እያጠባች የምታሳድግ፣ ፍቅርዋ በአጥንት እና በሥጋ ገብቶ የማይደመሰስ የሆነች እናት ማለት ነው:: ከልጅነት ጀምሮ ወንዙን፣ ተራራውን፣ ሜዳውን፣ ቆላውንና ደጋውን በማየት ስለሚታደግ አባቶች በሕህወትና በሞት የሰሩት ደግ ሥራ በአእምሮ ታትሞ ስለቀረ በሀገር እስካሉ ሲታይ፣ በስደት ሲሆኑ ሲታሰብ ፍቅርና ናፍቆት የሚያሳድር ሀገር ነው:: ሀገር አባት፣ እናት፣ ዘመድ፣ ምግብ፣ ጌጥና ሀብት በመሆኑ ድህንትና ጥቃት በመጣ ጊዜም ቢሆን እስከ ሞት ድረስ እንዲሠራበት ከአያት ከቅድም አያትና ከአባቶች በጥብቅ የተሰጠ ያደራ ገንዘብ ነው::” ይህ የሀገር
ምስጢር የተገለጸላቸው ሁሉ ዳር ድንበራቸውን ለማስከበር፣ መሰረታዊ የሆኑ ሀብቶችን፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጠቀሜታ ያላቸውን
ይዞታዎች ላለማጣት፣ ለልጆቻቸው መልካም ነገር ለማቆየት አጥንታቸውን ሲከሰክሱ፣ ደማቸውን ሲያፈሱ ኖረዋል፣ አሁንም በትጋት እየቀጠሉ
ነው:: ኢትዮጵያውያንም ይህንን የሀገር ምንነት በውል ተገንዝበውና ራሳቸውን ለሞት ሰጥተው ሀገራችንን ከታላቅ ኃላፊነት እና አደራ
ጋር አስረክበውናል::
ብዙ የሳይንስ ጥናቶች፣ የታሪክ እና ቅዱሳን መጻሕፍት፣ቅርሶችና
የተፈጥሮ ጸጋዎችዋ እንደሚያስረዱት እንዲሁም በዓይናችን እንደምናየው ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ሁሉ የተለየ የሚያደርጋት፣ ዜጎቿንም
የሚያኮራን እና ከሰራንም የሚለውጠን ብዙ ነገር በውስጧ አለ:: ከምንም ነገር በላይ ልናስተውለው የሚገባው የአየር ንበረትን፣ ውሃን
እና መልክዓ ምድርን ነው:: እነዚህ ሶስቱ በተስማሚ ሁኔታ ከተገኙ ህይወት ብዙም አስቸጋሪ አትሆንም:: ኢትዮጵያ “ዳሯ እሳት መሀሏ
ገነት” የሆነች ምስጢር ሀገር ነች:: በሰሜን ምስራቅ በአፋር ከሚገኘው ከኤርታሌ ጀምሮ፣ በኦጋደን፣ በሞያሌ፣ በጋምቤላ፣ በመተማ፣
በትግራይ የጠረፍ በረሀዎች ወዘተ ዙሪያዋን በበረሀ የተከበበች ስትሆን መሀሏ ግን ለኑሮ እጅግ ተስማሚ የሆነው ነገር ሁሉ የሞላባት
ልዩ ሀገር ነች:: እንዲህ ዙሪያውን ውሀ ቀጥሎ እሳት ቀጥሎ ገነታዊ ጸጋ የከበባቸው ሀገሮች በዓለማችን የሉም:: ይሁን እንጂ “ለሰሚው
ግራ” እንዲሉ ለዕለት ጉርሱ አጥቶ በረሀብ የሚገረፈው እና ሀገሩን ለቆ የሚሰደደው ሰው በሚሊየን የሚቆጠር ነው:: ይህ ጉዳይ ቁጭት
የማይፈጥርበት ኢትዮጵያዊ ስለሌለ ከችግሩ ለመውጣት ለየት ያለ የጋራ መግባባት እና ተነሳሽነት ያስፈልገናል በሚል ሞመንተም ለኢትዮጵያ
የሚል ዓለምአቀፋዊ ይዘት ያለው የረቀቀ እና የመጨረሻው የታላቅነት ሀሳብ በህዝባችን ውስጥ ለማስረጽ እና የሀገራችንን ህዳሴ ለማፋጠን
ከመንግስት ጎን በመሆን በግል ተነሳሽነት ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለመጀመር ታስቧል::
ከጥንት ጀምሮ የወዳጅ ጠላት የሆኑ የእኛን ድህነት እና ኋላቀርነት የሚፈልጉ ኃይሎች ያለማወቃችንን
ተጠቅመው አፍዘውን ኖረዋል:: ለምሳሌ ያህል ብንወስድ ግብጽ ከ300 ዓ ም (ከሶስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን) ጀምራ “ኢትዮጵያ ሹማምንቶቿን
ከግብጽ ታመጣለች” ይላል እና መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ የራሳችሁን ፓትርያርክ መሾም አትችሉም” በማለት ለ1600 (ለአንድ ሺ ስድስት
መቶ) ዓመት ያህል እስከ 1951 ድረስ 110 (በአንድ መቶ አስር) የግብጽ ጳጳሳት ኢትዮጵያን በእምነት ስም ገዝተዋታል:: እነዚያም
ጳጳሳት ህዝቡን በመንፈሳዊ ነገር ብቻ በመያዝ በአባይ እና በሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ተጠቅሞ እንዳይበለጽግ ወዳጅ እና መንፈሳዊ
መስለው ክፋታዊ የስጋ ስራ ሲሰሩ ኖረዋል:: ለጠላቶቻችን ሁሉ ድጋፍ በመስጠት እና እርዳታ በማስከልከል ልማታችን እንዳይፋጠን አሁን
ድረስ መሰናክል እየሆኑ ነው:: አቅም አግኝተን አባይን ገድበን ኃይል እናመነጫለን ብለን ብንጀምር ሰሞኑን የምታሰማው ማስፈራራት
ለዚህ ዋና ማስረጃ ነው:: “እናንተ ዝም ብላችሁ በረሀብ ሙቱ፣ እርዳታ አንጋጣችሁ እያያችሁ ኑሩ፣ እኔ ግን ገናናነቴን እንደያዝኩ
ዘለዓለም እቀጥላለሁ” እያለች ነው:: አሁን ዓይናችን እንደተገለጠ እና እኛም እንደ ሌላው ዓለም ለሀገራችን እና ለቀጣዩ ትውልድ
የምናስብበት ያስተሳሰብ ደረጃ መድረሳችንን የምናስመሰክርበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን የምንገልጽበት የብርሀን ዘመን ላይ
መድረሳችንን እናሳይ:: ሞመንተም ለኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ እና እንደ አድስ የመወለድ ሀሳብ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማስፋፋት ተነስቷል::
እናም እንኳን ደህና መጣህ ብላችሁ በመቀበል የአባቶቻችንን የእነ ኩሽን እና ፒያንኪን፣ የእነ አጼ ካሌብን እና አጼ ኢዛናን ኃያልነት
በዓይነ ህሌናችሁ እዩ፣ እንደእነርሱ በባህር ላይ በመርከብ ተንሳፈፉ፣ በአየር ላይ ብረሩ፣ ምድራችሁን በበረከት አትረፍርፉ፣ በኃያልነታችሁ
እርኩ::
ሞመንተም ምንድነው?
ሞመንተም (momentum) ጥሬ ቃሉ በፊዚክስ
የሳይንስ መስክ መጠነ ቁስ X በቶሎታ ነው (P = MV where
P = momentum, M = Mass and V = Velocity):: በሌላም መልኩ ሞመንተም “የእንቅስቃሴ ብዛት” (quantity
of motion) ይባላል:: ቃሉ በማህበራዊ ዘርፍም በዓለምአቀፍ ደረጃ ማህበራዊ ሞመንተም (Behavioral momentum) በመባል
ይታወቃል:: በቡድን ስፖርት፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖት፣ በሳይንስ እና በሌሎችም ህዝብን በጋለ መንፈስ ለጋራ ዓላማ ለማንቀሳቀስ ይጠቀሙበታል::
ያንን ዓለምአቀፋዊ ኃይል ወደ ሀገራችን አምጥተን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት መውጣት እና መበልጸግ ስለሚቻል ምስጢሩን ለመግለጽ
አስፈላጊ የሆኑ የሞመንተም ግብአቶች ተለይተው ሀሳቡን ለማስፋፋት ተጀምሯል:: የሀገርን እና የህዝብን ህዳሴ ግንባታ ለማፋጠን በውጭ
ጉዳይ ሚኒስተር በኩል የህዝብ ለህዝብ ድፕሎማሲ ወይንም የገጽታ ግንባታ አምባሳደር (public diplomacy/Image
building ambasaders) ለማቋቋም ሀገራዊ ንቅናቄ እያከናወነ ይገኛል:: ሞመንተም ለኢትዮጵያ የሚለውም የገጽታ ግንባታ
ክበብ የዚሁ የሀገር ገጽታ ግንባታ አካል ሆኖ በተለየ አቀራረብ እና ሂደት ህዳሴውን የማፋጠኛ አስተሳሰብ ነው::
ሞመንተም ለኢትዮጵያ ለምን አስፈለገ?
በአሁን ወቅት በመንግስትም ሆነ በግል መገናኛ
ብዙሀን እንደሚገለጸው ኢትዮጵያ ጫፍ እስከ ጫፍ ከልክ ባለፈ ህገ ወጥ ስደት ዜጎቿ በችግር በየበረሀው እያለቁ ነው:: ህገወጥ ስደቱም
ግለሰቦችን ለአደጋ ከማጋለጡ በተጨማሪ ከፍተኛውን ተጽእኖ የሚያሳርፈው በትምህርት እና በሀገር አጠቃላይ ገጽታ ላይ ነው:: ወጣቶቹ
ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርታቸውን እያቋረጡ ሲሄዱ በመማር ላይ ያሉትም ቢሆኑ ለሚቀጥለው ዓመት አለያም ሲመች ጊዜ ጠብቀው ለመሄድ
ስለሚያስቡ ትምህርት መማር እንደ መቆያ ብቻ እያዩት ይገኛሉ:: ከአንድ ትንሽ የገጠር መንደር እስከ 30 እና 40 ወጣቶች ተሰደው
ሄደው አዛውንቱ ያለ ጧሪ እና ያለቀባሪ ቀርተዋል:: ከፈተኛ እውቀት እና ክህሎት ያላቸውም ዜጎች ቢሆኑ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ
መሄጃ ሰበብ ካገኙ በዚያው ለመቅረት ያስባሉ@ ሄደው የቀሩትም በመቶ ሺወች የሚቆጠሩ ለመሆናቸው ያደባባይ ምስጢር ነው:: በተመሳሳይም አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ
በተለይም ትንሽ ፊደል የቆጠረው እንደ አውሮፕላን ክንፍ ቢታደለው በሮ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገሮች ለመሄድ ይፈልጋል:: ዳሩ ግን
ሀገራችን ከሌላው ሀገር ሁሉ በመምረጥ ፈልገን የምንኖርባት እንጂ መሄጃ ስላጣን ለጊዜው የምንቆይባት አይደለችም:: እኛ ግን ከዚህ
በተቃራኒው ወርቅ የሆነውን ጸጋችንን በቆሻሻ ሸፍነን የመዳብ ያህል ጸጋ የሌላቸው ሀገሮች ተሰደን ለመሰቃየት ማሰባችን ታላቅ ሀገራዊ
በሽታ ነው::
የዚህ ሁሉ ዋናው ምክንያት ከዘመን ዘመን የዘለቀው
እርስበርስ ያለመደማመጥ፣ የመፍራት፣ የመፍዘዝ፣ ራስን የመደበቅ፣ እውቀትን ያለማካፈል፣ ምሁራንን ያለማዳመጥ፣ ለጋራ ጉዳይ ዋጋ
ያለመስጠት እና ራስን ብቻ የመውደድ አስተሳሰብ ነው:: በተለይም ከ1960ወቹ ጀምሮ የተፈጠረው የኃይል እርምጃ ኃይል የሌለውን
ቡድን ፈሪ እንዲሆን አድርጎታል:: በፍርሀት ውስጥ ሆኖ ይህ ነው የሚባል ጥበብ ማፍለቅ እና ራስን መቀየር ከባድ ነገር ነው::
የወቅቱ የሀገራችን መንግስት እንደ መንግስት የሚችለውን ያህል ለማድረግ እና የሀገራችንን ህዳሴ ለማፋጠን እየጣረ እንዳለ ቢታወቅም
በጠቅላላው ህዝብ ውስጥ ግን ያንን ያህል የተንቀለቀለ እና ለለውጥ የጋለ ስሜት አይታይም:: በተለይም ምሁራን ዝም ብሎ ማየትን
እና መደበቅን መርጠዋል:: ምሁራን በተደበቁበት እና በሙሉ ኃይላቸው ሀገራቸውን ለመለወጥ በማይሰሩበት ሁኔታ የሚፈለገው ለውጥ በተፈለገው
ጊዜ ይመጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው::
እናም ከመንግስት ተጽእኖ ነጻ የሆነ፣ ከኃይል
የራቀ፣ ማንም የማይፈራው እና ማንንም የማያስፈራራ ነጻ የሆነ የህዝብ የውይይት መድረክ ቢፈጠር ፍርሀቱን ለማጥፋት እና ልማቱን
ለማፋጠን እንችላለን የሚል እሳቤ በመያዝ ይህን ሀሳብ ለማሳደግ ታስቧል:: ፍርሀት ስንል የሚፈራው ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ባለስልጣንም
የሆነ ህዝብን ስለሚፈራ ፍርሀቱ የሁላችንም በሽታ እንጂ የተወሰኑ ሰዎች ችግር ሊሆን አይችልም:: ፍርሀት ፍዘትን ይወልዳል፣ ፍዘት
ደግሞ ዓይን እያለን እንዳናይ፣ ጆሮ እያለን እንዳንሰማ፣ በችግር ውስጥ ሆነን ችግሩ እንዳይሰማን አድርጎናል:: በትንሹ ለምሳሌ
ብናነሳ በተለይም በከተማ ውስጥ በየሰፈራችን የተቆለሉ ቆሻሻወች እና የተጎሳቆሉ ህጻናት እና አዛውንቶች እያየን ችግሩን ለማቃለል
ያለመፋጠናችን የሚገርም ፍዘት እንዳለብን ማስረጃ ነው:: በዚህ በግሎባላይዜሽን ዘመን ዓለም እንደ መንኮራኩር እና አውሮፕላን እየተተኮሰ
በመረጃ እና በጥበብ እያጥለቀለቀን እኛ ግን ዝም ብለን በቆሻሻ ላይ መተኛታችን፣ የሚፈስ ወንዝ እና ለም አፈር በደጃችን እያለ
በርሀብ ምክንያት ወደ ሰሀራ በረሀ (ወደ ሱዳን እና ግብጽ) ስንሰደድ ይህ የሚገርም ፍዘት እንጂ ምን ይባላል? ሁሉን ነገር በዚች
ጽሁፍ መግለጽ ስለማይቻል ቀጣይ ውይይት እና የህዝብ ንቅናቄ በማድረግ ከፍርሀት ውጭ የሆነ፣ በእውቀት የተገነባ እና የበለጸገ ማህበረሰብ
ለመገንባት ጊዜው አሁን ሲሆን ኃላፊነቱም የእኛ መሆኑን እንወቅ::
ሞመንተም ለኢትዮጵያ
“እህ!”
ብየ እንደ እናቴ አምጫለሁ
“ዘራፍ!”
ብየም እንደ አባቴ ፎክሬለሁ
“ማን
አባቱ!” ብየ እንደ ሚስቴ ቀንቻለሁ
በእድሜየ
ሁሉ አልሜለሁ
ምኞቴን
አሁን አይቻለሁ
ሞመንተም
ለኢትዮጵያ አግኝቻለሁ::
የጌድዮን
ጸምር ተነጥፋ
የዳዊት
ወንጭፍ ተወንጭፋ
የአሮን
በትር ተወርውራ
ትንሽ
መስላ ኃይሏን አዝላ
ሰንኮፍን
እንደ በላችው ነጥላ
ሞመንተም
ለኢትዮጵያ መጥቷላ!!
ሰንካላውን
አስተሳሰብ የሚያጠራ
እጅግ
ታላቅ የሚያስፈራ
አይጨበጥ
አይዳሰስ የሚያጓራ
ለአንድ
ዓላማ የወረደ
በወገን
ፍቅር የነደደ
ስልጣኔ
ክብር ያደመቀ
ሞመንተም
ለኢትዮጵያ ተለቀቀ::
ጊዜው ከኛ ጋር ነው@ ነፋሱ የሚያግዘው ለኛ ነው@ ትንሽ ከተንቀሳቀስን የኢትዮጵያ ጥንታዊ ገናናነት በአጭር
ጊዜ ይመለሳል:: እናም ለሞመንተሙ መጀመር የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ወስነን እንነሳ@ሂደቱን በቀጣይ ውይይቶች የምናየው ይሆናል::
የሞመንተም ለኢትዮጵያ ክበብ አባላት እነማን
ናቸው?
ሞመንተም ለኢትዮጵያ ከዘር፣ ከሃይማኖት፣ ከጎሳ፣
ከፖለቲካ እና ከግል ጉዳይ ነጻ የሆነ ለእያንዳንዳችን ከግቦች በላይ የሆነ ግብ (super goal) ነው:: ፍቅርን፣ እምነትን፣
ሳይንስን፣ ክህሎትን እውቀትን እና ሌሎች መልካም ነገሮችን ሁሉ በማጣመር ለማንኛውም ሰው በሚስማማ መልኩ የተዘጋጀ እና ሀገርን
ለማበልጸግ የመጨረሻው የፍቅር አስተሳሰብ “ካቦ” ነው:: ስለሆነም የሞመንተሙ አባል መሆን የሚችለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነው::
ከአርሶ አደር እስከ ፕሮፌሰር፣ ከህጻን እስከ አዛውንት፣ ከሊስትሮ እስከ ፓይለት፣ ሴትም ሆነ ወንድ፣ ሁሉም ሰው አባል ነው::
እያንዳንዳንዱ ሰው የራሱ የህይወት ግብ አለው:: የግቦች ሁሉ ግብ ደግሞ ሀገርን በጋራ ማበልጸግ ሲሆን ከዚያ ለመድረስ ደግሞ ሞመንተም
ለኢትዮጵያ የያዘው ፍቅርን መሰረት ያደረገ የምስጢራት ጥምረት ዋናው ወርቃማ የገናናነት መንገድ ነው::
ይህን ሀሳብ ለማስፋፋት የተለያዩ መንገዶች የተቀየሱ
ሲሆን የመጀመሪያው የሞመንተሙን መጽሐፎች በተከታታይ መልቀቅ፣ ሁለተኛው
አርቲስቶችን በማሳተፍ ቪሲዲዎችን እና ድቪዲወችን እየሰሩ ለህዝብ ማዳረስ ሲሆን ከዚያው ጎን ለጎን እያንዳንዱ ግለሰብ በግል ተነሳሽነት
ሀሳቡን በአቅራቢያው ካለው ወገኑ ጋር በመነጋገር የጋራ ሀሳብ መያዝ ይሆናል:: ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም፣ የመንግስት መስሪያ
ቤት በተለይም ትምህርት ቤቶች፣ እድሮች፣ ማህበራት፣ መንግስታዊ ያልሁኑ ድርጅቶች፣ ድረ ገጾች ወዘተ የሞመንተሙን ሀሳብ ለማስፋፋት
እንጠቀምባቸዋለን:: አንድ የሆነ የሞመንተም ስነ ልቦና ካዳበርን
በኋላ ወደ እውነተኛው የልማት እና የብልጽግና ጎዳና እንገባለን:: ያን ጊዜ አንድ ቀን የሚፈጀውን ስራ በአንድ ሰዓት፣ አንድ ዓመት
ሊፈጅ የሚችለውን ስራ በአንድ ወር፣ መቶ ዓመት ሊፈጅ የሚችለውን ስራ በአስር ዓመት በመጨረስ ወደማይታመን የጥበብ እና የስልጣኔ
ደረጃም ባልተጠበቀ ጊዜ መድረስ እንችላለን:: ሞመንተም 1+1 =
2 በሚለው ደረቅ የሳይንስ ቀመር አይሰራም:: በረቂቅ ኃይል እየሰራ አውሮፕላንን የሚያበረው፣ መንኮራኩርን የሚያስፈነጥረው እና
እንዲሰራ እገዛ ያደረገው የስልጣኔ እና የጥበብ ሁሉ መሰረት የመጨረሻው ምስጢር ነው::
ሞመንተም ለኢትዮጵያ!
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ገናናነት በአጭር ጊዜ ይመለሳል
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ